በዶክተር ቦጋላች መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል ለተገልጋዩ ህብረተሰብ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ እንቅሰቃሴዎች ተጠናክሮ መቀጠል አለባቸው ተባለ። በከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በክቡር አቶ አረጋ እሸቱ የተመረ የሆስፒታሉ ቦርድ አባላት የሆስፒታሉን የስድስት ወር የሥራ እንቅስቃሴ ገምግመው ቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውም ተመልክቷል። በዶክተር ቦጋላች መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል የሥራ እንቅስቃሴን የገመገሙት የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የሆስፒታሉ የቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ አረጋ እሸቱ በሆስፒታሉ የተገልጋዩን ህብረተሰቡ እርካት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸው ገልፀዋል። በሆስፒታሉ ተገቢውን የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ጤናማና አምራች ዜጎችን እንዲፈጠሩ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን የገለፁት ክቡር ዋና አስተዳዳሪው ለዚህም የሆስፒታሉ ሠራተኛ ተገቢውን የሙያ ስነ ምግባር በመላበስ ህብረተሰቡን በቅንነት ማገልገል እንዳለበትም አሳስበዋል። መንግስት በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በማረምና በማስተካካል በተለይ በጤና ተቋማት የሚስተዋሉ የመድኃኒትና ሌሎችም አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት ህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት እንዲችል በትኩረት እየተሠራ መሆኑ የተናገሩት ክቡር አቶ አረጋ እሸቱ በዚህም በዶክተር ቦጋለች መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን በማፋጠን ህብረተሰቡ ተገቢውን የጤና አገልግሎት በአቅራቢያው እንዲያገኝ በትኩረት ይሠራልም ነው ያሉት። በሆስፒታሉ የተገለፁ ተግዳሮቶችን በመለየትና በየደረጃው እንዲፈቱ የየድርሻችንን ወስደን መስራት ይገባል ያሉት ክቡር ዋና አስተዳዳሪው ለህብረተሰቡ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በተለይ ከማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልገሎት /ማዐጤመ/ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው ካሉ መዋቅሮች ጋር በመነጋገርና የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ የሆስፒታሉ አገልግሎት ለአፍታም እንዳይስተጓጎል በቅንጅት መሥራት ይገባልም ነው ያሉት። የከምባታ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ራመቶ አቦ በጤናው ሴክተር እያገጠሙ ያሉ የግብዓት ማነቆዎችን በመሻገር ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ አፈፃፀም እየተመዘገበ መሆኑን በመጥቀስ እናቶች ከ12 ሳምንት በፊት ክትትል በመጀመር ለፅንሱም ለእናትም ጠቃሚ በመሆኑ በጊዜ ቅድመ ወሊድ መጀመር አስፈላጊ ነው ብለዋል:: የእናቶችና የህፃናት ጤና ለመጠበቅ በትኩረት መስረት ወሳኝ በመሆኑ ተገቢውን ክትትል እንዲያደርጉ የግንዛቤ መፍጠር ሥራ መጠናከር እንዳለበትም አሳስበዋል። የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መዲህን ተግባር አፈፃፀማችንን ከፍ በማድረግ በዘርፉ በተዋረድ የሚገኘውን ድጋፍ ህብረተሰባችንን ተጠቃሚ እንዲሆን በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን ከጤና ተቋማት ባሻገር ቤት ለቤት በመስጠት ብሎም የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን በየአካባቢው በህብረተሰብ ተሳትፎ በመገንባት የመድኃኒት እጥረት ችግር ለመቅረፍ በቅንጅት መሠራት አለበትም ብለዋል። ሆስፒታሉ እንደ ሀገር የተቀመጠውን ስታንዳርድ በማሟላት ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል ለማድረግ በሆስፒታሉ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች ተጠናክሮ መቀጠል አለባቸውም ነው ያሉት። የዶክተር ቦጋለች መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ደረበ ዮሐንስ በበኩላቸው የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በሆስፒታሉ ማናቆ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት በማረምና አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን የተገልጋዩን ህብረተሰቡ እርካታ ለማረጋገጥ ከዞኑ መንግስትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል። የሆስፒታሉ አገልግሎት ለአፍታም እንዳይቋረጥ የሆስፒታሉ ማህበረሰብ ለማገልገል በከፍተኛ ትጋትና ቁርጠኝነት ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝና ከወረቀት ነፃ አገልግሎት /የEMRI/ ተግባራዊ መደረጉን ገልፃው ህብረተሰቡን ከከፍተኛ ወጪና እንግልት ለማዳን ብሎም የአገልግሎት ደረጃውን ከፍ ለማድረግ የኦክስጅንና የሲቲ ስካን ተካላ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቃቀቸውን ነው ዶክተር ደረበ አክለው የገለፁት። በመርሃ ግብሩ ላይ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሲሳይ ታገሠን ጨምሮ የሆስፒታሉ የሥራ ኃላፊዎች እና የሆስፒታሉ ቦርድ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።