Skip to main content
news5

የዶክተር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታልን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ። በከምባታ ዞን የዱራሜ ከተማ አስተዳደር የዶክተር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታልን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ:: የሆስፒታሉ ተገልጋዮች በበኩላቸው አሁን ላይ እየተሰጠ ባለው አገልግሎት ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል። የዶክተር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አያኖ ኤልያስ እንደገለጹት ከካርድ ክፍል ጀምሮ የእናቶች ወሊድ አገልግሎትን ጨምሮ የድንገተኛ፣ ተመላላሽና ተኝቶ ህክምና አገልግሎት በሆስፒታሉ ስፔሻሊስት ሀኪሞች በተሟላ የላቦራቶሪ ምርመራ እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል። የኤሌክትሮኒክ ሜዲካል ወይም የመረጃ አያያዝ ስርዓት ዘመናዊ እንዲሆን ሁሉንም አገልግሎቶች ዲጅታል ለማድረግ ሂዳት ላይ መሆኑንም ዶክተር አያኖ ጠቁመዋል:: ሆስፒታሉን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጥረት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት እንዲደግፉ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ዶክተር አያኖ ጥሪ አቅርበዋል። የዶክተር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ደረበ ዮሐንስ ሆስፒታሉ የህክምና አቅሙን በማጎልበት ከዚህ ቀደም ያልተጀመሩ የህክምና አገልግሎቶችን ብቃት ባለው የሰው ኃይል በመታገዝ በተደራጀ መልኩ ጥራት ያለውን የጤና አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ከመድኃኒት አቅርቦት አኳያ የሚስተዋሉ የመድኃኒት እጥረት ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ጠቅሰዋል። የአገልግሎት ጥራትና ውጤታማነትን በማሳደግ በቀጣይ የሆስፒታሉን አቅም ይበልጥ በማጎልበት የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በ"ኤም.አር.አይ" እና በ"ስቲ ስካን" የታገዘ ህክምና ለመስጠት ቁሳቁሶች በተገቢ እየተሟሉ እንደሆነም ተጠቅሷል። በቀጣይ የታካሚዎችን እንግልት ለማስቀረት የፌስቱላ ህክምና አገልግሎት ለማስጀመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ዶክተር ደረበ አመላክተዋል። በሆስፒታሉ የላብራቶሪ ባለሙያና የክፍሉ አስተባባሪ የሆኑት መሰለ ጌታቸው እንዳሉት የምሳ ሰዓትን ጨምሮ ቀንም ሆነ ማታ እየገቡ ለታካሚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ሙያዊ ግዴታቸውን በተገቢ እየተወጡ እንደሆነ ጠቅሰዋል። በሆስፒታሉ ያነጋገርናቸው አንዳንድ አስተያት ሰጪዎች እንዳሉት አሁን ላይ በሆስፒታሉ እየተሰጠ ባለው አገልግሎት ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።