Skip to main content
news12

በዶክተር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል የኦክስጅን ማምረቻ ማእከል ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ፣ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አንተነህ ፍቃዱ እና የማእከላዊ ኢትዮጵያ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በተገኙበት የዶክተር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል የኦክስጅን ማምረቻ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡ ሲሆን በሆስፒታሉ የሲቲ እስካን አገልግሎትም በይፋ አስጀምረዋል። በማስጀመሪያ መርሀግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ በክልሉ የጤናው ዘርፍ የሚያሻግሩ ለውጥ የሚያመጡ ስራዎች እየተሠሩ እንዳሉ ገልጸዋል። ዶክተር ደረጀ የተጀመሩ ግንባታዎቹ በቶሎ ተጠናቀው ሌሎችም እንዲጀመሩ በማሳሰብ ጤና ሚኒስቴር ድጋፉን እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። የሲቲ ስካን አገልግሎት በሆስፒታሉ መጀመሩ ትልቅ ለውጥ ነው ያሉት የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ አንተነህ ፍቃዱ በዛሬው እለት በሆስፒታሉ የጀመሩት ስራዎች የህብረተሠቡን ችግር የሚፈቱ እንደሆኑ በመጠቆም ስራዎቹ ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ክልሉ የተሞክሮ ማእከል ለማድረግ እየሰራን ነው ያሉ ሲሆን ለዚህም ድጋፍ ያደረጉ ጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች አካላትን አመስግነዋል። በተያያዘም ቡድኑ በከንባታ ዞን የሚገኙት የሺንሺቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና የዶክተር ቦጋለች ገብሬ መታሠቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ በሀላባ ዞን የሚገኘው የሀላባ ቆሊቶ አጠቃላይ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸውም በሆስፒታሉቹ የሚገኙ የጽኑ ህክምና ክፍል፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የተመላላሽ ታካሚዎች ክፍል፣ የእናቶችና ህጻናት ክፍል ግንባታዎች፣ የቀዶ ህክምና ማስፋፋፊያ ግንባታዎች፣ የኤምዲአር ቲቢ ህክምና ማእከል ግንባታ፣ የኦክስጅን ማከፋፈያ ማእከል እና የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ተመልክተዋል።