የዶ/ር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል የተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ማዕከል ዕውቅና አገኘ። የዶ/ር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል የተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ማዕከል (CPD-Center) የዕውቅና ፈቃድ ሰርተፍኬት (CPD Accreditation) ከኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ማግኘቱን አሳውቋል። የተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ማዕከሉ የዕውቅና ፈቃድ ሰርተፍኬት ያገኘዉ ከፌዴራል ጤና ሚነስትር ለCPD ማዕከላት ዕዉቅና የመስጠት (CPD Accreditor) ፈቃድ ባለዉ የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር አማካይነት በተደረገዉ ተከታታይ ምዘና መሰረት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ ማዕከሉ የሚጠበቀዉን እስታንዳርድ ሙሉበሙሉ ማሟላቱን በምዘናዉ የተረጋገጠ መሆኑም ተገልጿል። የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ደረበ ዮሐንስ በፌዴራል ጤና ሚንስቴር በተረጋገጡና ዕዉቅና በተሰጠባቸዉ ኮርሶች ላይ የተለያዩ የሥልጠና አሰጣጥ ዘዴዎችን በመጠቀም ሠልጣኞች በሥልጠና ወቅት በሚደረገዉ ምዘናና የኮርስ ይዘት በተቀመጠዉ እስታንደርድ መሠረት በተቀናጀዉ የሰዉ ሀብት መረጃ አስተዳደር (i-HRIS) ሥርዓት የክሬዲት የምዘና ሰርተፊኬት በመዉሰድ የሙያ ፈቃዳቸዉን ለማሳደስ መጠቀም የሚችሉ መሆኑ ገልጸዋል፡፡ በዞኑ እና በአጎራባች አከባቢዎች የሚገኙና በጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች የተሰማሩ የመንግሥትና የግል ተቋማት የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን፤ወርክሾፖችን እና ስብሰባዎችን ለማካሄድ ሲያቅዱ ከሆስፒታሉ የተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ማዕከል (CPD Provider Center) ጋር በቅንጅት ቢሰሩ ይበልጥ ዉጤታማ መሆን ስለሚችሉ በማዕከሉ እንዲገለገሉ ዶ/ር ደረበ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። በመጨረሻም ዶ/ር ደረበ ዮሐንስ ሆስፒታሉ ለዚህ ስኬት እንዲበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉትን የባለድርሻ አካላት አመስግነዋል።