በከምባታ ጠምባሮ ዞን ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል ዱራሜ በእናቶችና ህፃናት ህክምና ማዕከል አንዲት እናት ሦስት ወንድ ልጆችን በሠላም ተገላገለች። ሦስቱም ሕፃናት በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል። የሕፃናቱ እናት ወይዘሮ ትግስት ሎዳሞ እንደተናገረችው ከእርግዝና ወቅት ጀምሮ የሕክምና ማዕከሉ ባለሙያዎች ተገቢውን ክትትል ያደርጉላት የነበረ ሲሆን በወሊድ ወቅትም በተደረገላት በባለሙያዎች እገዛ ሦስት ልጆችን በሰላም በምጥ መገላገሏን ገልፃለች። ለመውለድ ከገባችበት ሰዓት ጀምሮ የሕክምና ማዕከሉ ሐኪሞች እና አዋላጅ ነርሶች ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እንዳደረጉላት የገለፀችው ወ/ሮ ትግስት ሎዳሞ ለተደረገላት አገልግሎትም መላውን የተቋሙን ባለሙያዎች አመስግናለች። የዛሬዎቹን ሦስት ወንድ ልጆች ጨምሮ የአራት ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮ ትግስት ሎዳሞ ከዚህ በፊት መንታ ወልዳ እንደማታውቅና አሁን ሦስት ልጆችን በሰላም መገላገሏ እንዳስደሰታት ተናግራለች። የወይዘሮ ትግስት ሎዳሞ ባለቤት አቶ ብርሀኑ ጴጥሮስ በበኩላቸው ባለቤታቸው ከእርግዝና ወቅት ጀምሮ በተቋሙ ተገቢውን ክትትል ስታደርግ እንደነበር አውስተው በወሊድ ወቅትም የሆስፒታሉ ባለሙያዎች በተሻለ ሙያዊ ስነምግባር ለባለቤታቸው ተገቢውን የህክምና በመስጠታቸው ባለቤታቸው ያለምንም ችግር በሰላም ሦስት ልጆችን መገላገላቸውን ገልፀዋል። እንደ አቶ ብርሀኑ ጴጥሮስ ገለፃ ባለቤታቸው በተቋሙ ያለምንም ክፍያ በነፃ ተገቢውን የወሊድ አገልግሎት ማግኘታቸውን በመግለፅ በወቅቱ በተቋሙ የእጅ ጓንት ባለመኖሩ ከውጭ መገዛታቸውን ግን ገልፀዋል። በዶክተር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል የእናቶችና ህፃናት ህክምና ማዕከል አስተባባሪ እና የፅንስና ማህፀን ስፔሻሊስት ዶክተር አብነት አዳነ ተቋሙ አንድም እናት በወሊድ ምክንያት መሞት የለባትም በሚል መርህ ለእናቶች ነፃ የወሊድ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልፀዋል። ማዕከሉ ለበርካታ እናቶች ያለምንም ክፍያ ተገቢውን የወሊድ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የገለፁት ዶ/ር አብነት አዳነ እንዲህ አይነት ከሁለት በላይ የሆኑ መንትዮች መወለዳቸው አልፎ አልፎ የሚፈጠር ነገር መሆኑንም አብራርተዋል። ማዕከሉ በሚሰጠው አገልግሎት ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ በዞኑና አጎራባች ዞኖች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ያሉት ዶ/ር አብነት አዳነ ተቋሙ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የግብዓት እጥረቶች እያጋጠሙት በመሆኑ ኅብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።